የኢትዮጵያን አይሲቲ ታለንትና ኢኖቬሽን ስነምህዳር ለማሳደግ በሚዘጋጀው አመታዊ የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ከ30 በላይ ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጡ 63 ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ፡ ታኅሣሥ 21፣ 2015 ዓ.ም።  የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ለአለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚዘጋጅና የአይሲቲ ታላንት ስነ ምህዳር ጤናማ እድገትን የሚያበረታታ እና የኢንዱስትሪ እና የትምህርት ውህደትን የሚደግፍ ነው።

የ2022-2023 እ.ኤ.አ አመታዊ ሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ታህሳስ 18 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኢትዮጵያ የተካሄደ ሲሆን ከ30 በላይ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች እና የግል ኮሌጆች ትምህርታቸውን የሚከታተሉ 63 ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

በ5ኛው ዙር አመታዊ ሀገር አቀፍ ውድድር ከኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግ፣ ከኮምፒውተር ሳይንስ፣ ከሶፍትዌር ኢንጂነሪንግ፣ ከኮሚዩኒኬሽን ኢንጂነሪንግ እና ከአይሲቲ ትምህርት ክፍሎች የተውጣጡ ተማሪዎች ተወዳድረዋል። ውድድሩ 3 ምድቦች ያሉት ሲሆን እነዚህም ክላውድ፣ ኔትወርክና ኮምፒውቲንግ  (Network, Cloud and Computing) ናቸው፡፡

ከ1300 በላይ ተማሪዎች የመጀመሪያ ፈተናውን በኦንላይን  በታህሳስ 10 ቀን 2015 ዓ.ም የወሰዱ ሲሆን ከመካከላቸው 63ቱ ብቻ ወደ ቀጣዩ የሀገር አቀፍ ደረጃ ውድድር አልፈዋል። እነዚህ ተማሪዎች በሀገር አቀፍ ውድድር የተሳተፉ ሲሆን 15ቱ ፈተናውን አልፈው በሪጅን ደረጃ በሚካሄደውና ከ20 በላይ ሀገራት ወደሚሳተፉበት ውድድር አላፊ ሆነዋል፡፡

የ2021 – 2022 እ.ኤ.አ የሁዋዌ አይሲቲ ግሎባል የመጨረሻ ውድድር አሸናፊዎች ህዳር 02 ቀን 2015 ዓ.ም የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ በተገኙበት እውቅና ማግኘታቸውና የዘንድሮ ውድድር በይፋ መጀመሩ ይታወሳል፡፡

የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር በአለም አቀፍ ደረጃ በሁዋዌ ICT አካዳሚዎች እና በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የአይሲቲ አካዳሚውን መቀላቀል ለሚፈልጉ ተማሪዎችና ለተቀላቀሉ ተማሪዎች የተዘጋጀ ነው። ሁዋዌ  ውድድሩን ሲያዝጋጅ ተማሪዎች የሚወዳደሩበት እና ሀሳብ የሚለዋወጡበት ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢ እንዲኖራቸው በማድረግ የአይሲቲ እውቀታቸውን እና የተግባር ክህሎቶቻቸውን በማሻሻል አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እና መድረኮችን በመጠቀም አዳዲስ ነገሮችን የመፍጠር አቅማቸውን ለማሳደግ ነው።

ከ2015 እ.ኤ.አ ጀምሮ የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር ተፅእኖ በተሳታፊዎች ቁጥር እያደገ የመጣ ሲሆን የባለፈው አመት 6ኛው አለም አቀፍ የሁዋዌ አይሲቲ ውድድር 150,000 ተማሪዎች በ85 ሀገራት እና ሪጅኖች ከ2,000 በላይ ዩኒቨርስቲዎችና ኮሌጆች ተሳትፈውበታል።  ከ2017 እ.ኤ.አ ጀምሮ በኢትዮጵያ በየዓመቱ እየተካሄደ ይገኛል።

leave a reply